ዜናዎች | 14.03.2010 | 13:00 UTC
የሶማሊያ ጦር ፍቱን አይደለም ተባለ
የሶማሊያ መንግሥት ጦር ዓለምአቀፍ ድጋፍ ቢሰጠውም ፍቱንነት የጎደለው፣ በሚገባ ያልተደራጀና ሙስና የሰፈነበት እንደሆነ የአገሪቱን ሁኔታ የሚታዘበው የተባበሩት መንግሥታት ቡድን አመለከተ። ጦሩ ለሕልውናው ወደፊትም በውጭ ወታደሮች ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሆኖ እንደሚቀጥልም ተጠቅሷል። የተባበሩት መንግሥታት ታዛቢ ቡድን ዘገባውን በፊታችን ሣምንት ለጸጥታው ም/ቤት እንደሚያቀርብ እየተጠበቀ ነው። እሥላማዊው የዓመጽ ቡድን አል-ሻባብ በወቅቱ አብዛኛውን የሶማሊያን ማዕከላዊና ደቡባዊ ክፍል የሚቆጣጠር ሲሆን የሽግግሩ መንግሥት በአንጻሩ በሞቃዲሾ ጥቂት አካባቢዎች ተወስኖ እንደሚገኝ ይታወቃል። ታዛቢው ቡድን በዘገባው እንዳመለከተው ወታደራዊ መፍትሄ የጠፋው በተቃዋሚው ወገን ጥንካሬ ሣይሆን በሽግግሩ መንግሥት ድክመት የተነሣ ነው። ቡድኑ የሶማሊያ መንግሥት ለሕልውናው የአፍሪቃን ሕብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አሚሶምን ማመስገን እንዳለበትም አስረድቷል። ይህ በዚህ እንዳለ በመሬትና በውሃ ይዞታ በማዕከላዊው ሶማሊያ በተነሣ የጎሣ ግጭት ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸውን ከሮይተርስ የተገኘ ዜና አመልክቷል። ታዛቢው ቡድን ያለፈውን 2009 ዓ.ም. አስመልክቶ ባወጣው ዘገባው ኤርትራ ለሶማሊያ ዓማጺያን የፖለቲካ፣ የዲፕሎማቲክ፣ የፊናንስና ወታደራዊ ዕርዳታ መስጠት ቀጥላ እንደነበርም ገልጿል። ሆኖም በተጨማሪ እንደተነገረው በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ የኤርትራ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ አይቁም እንጂ ብዙም ጎልቶ አይታይም።








